loading
አልበሽር ፖሊሶቻቸውን ያልተመጣጠነ ሀይል እንዳይጠቀሙ አሳሰቡ

የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር ህዝባቸው በአስቸኳይ ከስልጣን እንዲወርዱ በተቃውሞ ፋታ ቢነሷቸወም፤ ፖሊሶቻቸው በሰልፈኞቹ ላይ ከልክ በላይ ሀይል እንዳይጠቀሙ መክረዋቸዋል፡፡

አልበሽር ከፖሊስ ሀላፊዎች ጋር ባደረጉት ውይይት የሱዳንን ህዝብ ህይወትና ንብረት የመጠበቅ ሀላፊነት አለብን፤ ቢቃወሙንም ጉዳት እንዲደርስባቸው አንፈልግም ብለዋል፡፡

ፖሊስ በበኩሉ የመንግስት ለውጥ የሚካሄደው በምርጫ ብቻ ነው፤ በሀይልና በብጥብጥ ይህን ለማስቀየር የሚሞክር ካለ ሀላፊነቱን ራሱ ይወስዳል የሚል መግለጫ አውጥቷል፡፡

ሚድል ኢስት ሞኒተር እንደዘገበው የሱዳን የሀገር ውስጥ ሚኒስትር አህመድ ቢላል የሀገሪቱ ፖሊስ ከፕሬዝዳንት አልበሽር ጎን እንደሚቆም በይፋ ተናግረዋል፡፡

ይሄ ደግሞ የአልበሽር እና የባለ ስልጣኖቻቸው ሀሳብ የተለያየ መሆኑን አሳይቷል ነው የተባለው፡፡

የፖሊስ ዳይሬክተር ጀኔራሉ አል ጣይብ ባቢኪር የህዝብን ንብረት ማውደም  ትክክለኛ ተቃውሞ አይደለም፤ ነገሩን ውስጥ ለውስጥ የሚያባብሱትን አድነን ለፍርድ እናቀርባቸዋለን ብለዋል፡፡

ነገሩ ያሳሰበው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሀገሪቱ የተከሰተው አለመረጋጋት በጥንቃቄ እንዲያዝ ለሱዳን መንግስት ጥሪ አቅርቧል፡፡

የድርጅቱ ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ሰዎች ሀሳባቸውን በነፃነት የመግለፅ መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል፤ የሞቱና ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦች ጉዳይም በአስቸኳይ መጣራት አለበት ሲሉ በቃል አቀባያቸው በኩል መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

እስካሁን በግጭቱ ሳቢያ 19 ሰዎች ሞተዋል ቢባልም የተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን ይህን ቁጥር ወደ 40 ያደርሱታል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *