ተናሰባቹ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አንድ የምርጫ ደህንነት ባለስልጣንን አባረሩ::
አዲስ አበባ፣ ህዳር 09፣ 2013 ተናሰባቹ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አንድ የምርጫ ደህንነት ባለስልጣንን አባረሩ:: ምርጫው ተጭበርብሯል በሚለው አቋማቸው የጸኑት ትራምፕ የሳይበር እና መሰረተ ልማት ደህንነት ሃላፊ የነበሩትን ክሪስ ክሬብን ነው ያባረሯቸው፡፡ ለክሬብ መባረር ምክንያት የተባለው ደግሞ የዘንድሮው ምርጫ በአሜሪካ ታሪክ ካለፉት ምርጫዎች ሁሉ አስተማማኝና ተዓማኒ ነው የሚል ከትራምፕ በተቃራኒ የቆመ አስተያየት በመስጠታቸው ነው፡፡
ትራምፕ በሰጡት ማብራሪያ ክሬብን ያባረርኩት በርካታ ሀሰተኛ መግለጫዎችን ከመስጠት አልቆጠብ በማለቱ ነው ብለዋል፡፡ ቢቢሲ በዘገባው እንዳስነበበው ክሪስ ክሬብ ከመከላከያ ሚኒስትሩ ማርክ ኤስፐር ቀጥለው የተባረሩ ሁለተኛው የፔንታጎን ሰው ናቸው፡፡ ይህም ትራምፕ በተወሰኑ የመከላከያ ባለስልጣናት ላይ እምነት ማጣት ጀምዋል የሚለውን አባባል ያጠናክረዋል ነው የተባለው፡፡
ይሁን እንጂ ክሬብ ሊባረሩ የሰዓታት እድሜ ሲቀራቸው በተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ድምፅ ወደ ባይደን እንዲቀየሩ ተደርጓል የሚል ጽሁፍ በትዊተር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል ተብሏል፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ከአሁን ቀደም የለጠፏቸው ጽሁፎችን ጨምሮ ሌሎች ፅሁፎቻቸውም ተነስተዋል፡፡ የተመራጩ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ቃል አቀባይ ክሬብ ምርጫውን በታማኝነት በመጠበቃቸውና እውነቱን በመናገራቸው ሊሸለሙ እንጂ ሊባረሩ አይገባም ሲሉ ደግፈዋቸዋል፡፡