loading
በድሬዳዋ ሲካሄድ የቆየው የሶማሌ ክልል የህዝብ ተወካዮች የጋራ የምክክር መድረክ የህዝቦችን ሃሳብ ያንጸባረቀ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ።

በድሬዳዋ ሲካሄድ የቆየው የሶማሌ ክልል የህዝብ ተወካዮች የጋራ የምክክር መድረክ የህዝቦችን ሃሳብ ያንጸባረቀ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ።

ለሶስት ቀናት በቆየውና የሶማሌ ክልል ህዝብ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ አጀንዳውን አድርጎ ሲካሄድ የቆየው ስብሰባ ባለ 7 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል።
የክልሉ የህዝብ ተወካዮች በክልሉ በሰው ህይዎት እንዲሁም በመንግስት ንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን በመግለጽ ድርጊቱ በአስቸኳይ ሊቆም እንደሚገባ አሳስበዋል።
የእምነት ተቋማት በተለይም ቤተ ክርስቲያን እየተቃጠለና የመልካም አስተዳደር ጥያቄን ያነሱ ወጣቶችም እስርና እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑንም ተወካዮቹ በምክክር መድረኩ ላይ ጠቅሰዋል።
አሁን ላይ ክልሉን እየመራ ያለው አስተዳደርም ስልጣኑን ለማርዘም ከጎረቤት አካባቢዎች ጋር ህዝቡን በማጋጨት የአካባቢውን ሰላም ለማደፍረስ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከዚህ ባለፈም በክልሉ የመልካም አስተዳደር ጥያቄን የሚያነሱ ወጣቶችን ማሰር፣ ማሰቃየት፣ መግደልና ሌሎች ከፍተኛ ሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየፈጸመ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
የኢፌዴሪ መንግስትም የክልሉን ህዝብ ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ በክልሉ የነበረውን ተከባብሮና ተዋዶ የመኖርን ባህል ወደ ብሄር ግጭት በመጠምዘዝ ከሌላ ክልል ተወላጆች ጋር ግጭት ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ አካላት ተይዘው ለህግ ሊቀርቡ ይገባልም ብለዋል።
እስካሁን በክልሉ ለተከሰተው አለመረጋጋት እና ለሰው ህይወት መጥፋት ዋነኛ ተጠያቂ የክልሉ ባለስልጣናት በመሆናቸው እነርሱን በቁጥጥር ስር በማዋል ህዝባዊ መሰረት ያለው መንግስት እንዲቋቋምም ጠይቀዋል።
የክልሉ አመራርም ህዝቡን የመምራት ብቃት ስለሌለው በአስቸኳይ ስልጣን ሊለቅ ይገባል ያሉት የህዝብ ተወካዮቹ፥ መንግስትም ጣልቃ በመግባትና የአካባቢውን ሰላም ወደነበረበት በመመለስ ወንጀለኞችን ለፍርድ እንዲያቀርብም ነው የጠየቁት።
በክልሉ አላግባብ በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎችን ከእስር ነጻ በማውጣትና ክልሉን ከኦሮሚያ ጋር በሚያዋስኑት ወረዳዎች የሚከሰቱ ግጭቶችን በማስቆምም ከድርጊቱ ጀርባ ያሉ ወንጀለኞች ለፍርድ ሊቀርቡ ይገባልም ነው ያሉት።
አሁን ላይ ያለው አስተዳደር ስልጣኑን ለቆ ህዝባዊ መሰረት ያለው መንግስት እስከሚቋቋም ድረስም ለ2011 ዓ.ም የተመደበው የክልሉ በጀት እንዳይለቀቅም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የክልሉ ልዩ ሃይልም ከህዝባዊ ወገንተኝነት በተቃረነ መልኩ እየፈጸመ ያለውን ኢ – ህገመንግስታዊ ድርጊት፥ የፌደራል መንግስት በአስቸኳይ ሊያስቆም እንደሚገባም በአቋም መግለጫቸው አስታውሰዋል።
(ኤፍ ቢ ሲ)

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *