በዱባይ ማራቶን በወንዶች አትሌት ጌታነህ ሞላ ክብረወሰን በማሻሻል በድል አጠናቅቋል
በዱባይ ማራቶን በወንዶች አትሌት ጌታነህ ሞላ በድል አጠናቅቋል
የዓለማችን ውዱ የማራቶን ውድድር ዛሬ ማለዳ ተካሂዷል፡፡
ለአሸናፊ አትሌቶች ውድ ገንዘብ በመስጠት የሚታወቀው የስታንዳርድ ቻርተርድ ዱባይ ማራቶን 2019፤ 20ኛ ውድድሩ ዛሬ ማለዳ ተከናውኖ በወንዶች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተከታትለው በመግባት ድል አድርገዋል፡፡
አትሌት ጌታነህ ሞላ በ2፡03፡34 በመግባት ውድድሩን በቀዳሚነት ከማጠናቀቁ በተጨማሪ ባለፈው የቦታውን ክብረወሰን በማሻሻል ያሸነፈውን የሀገሩን ልጅ ሞስነት ገረመው የ2፡04፡00 ሰዓት በማሻሻል ነው፤ ሌላኞቹ ኢትዮጵያውያን ሄርጳሳ ነጋሳ በ2፡03፡40 ሁለተኛ፣ አሰፋ መንግስቱ በ2፡04፡ 24 ጊዜ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድራቸውን ፈፅመዋል፡፡
ኬንያዊው ኢማኑኤል ኪፕኪምቦይ አራተኛ፤ ኢትዮጵያውያኑ ሽፈራ ታምሩ፣ ከልክሌ ገዛህኝ፣ አዱኛ ታከለ፣ ብርሃኑ ተሾመ እና ፍቃዱ ከበደ እስከ ዘጠኝ ያለውን ደረጃ ሲይዙ፤ በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ሲውዘርላንዳዊው ታደሰ አብርሃም አስረኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቅቀዋል፡፡
በሴቶች የተደረገውን ውድድር ኬንያዊቷ አትሌት ሩት ቼፕጌቲች በ2፡17፡08 ጊዜ በመግባት በኢትዮጵያዊቷ ሮዛ ደረጀ የተያዘውን 2፡19፡17 ሰዓት በማሻሻል ጭምር ቀዳሚ ሁና አጠናቅቃለች፤ በዚህም ኢትዮጵያውያን ሴት አትሌቶች ለ12 ዓመታት ይዘውት የቆዩትን የበላይነት ገትታለች፡፡
በዱባይ ማራቶን ለመጨረሻ ጊዜ ድል ያደረገችው ኬንያዊት አትሌት ደሊላህ አሲያጎ ስትሆን በ7ኛው የ2006 ማራቶን 2፡43፡09 በሆነ ጊዜ በመግባት አጠናቅቃለች፡፡ ቼፕጌቲች ያስመዘገበችው ሰዓትም ከፓውላ ራድክሊፍ እና ሜሪ ኪታኒ በመቀጠል ሶስተኛው የዓለም የማራቶን ሪከርድ ሁኗል፡፡
የ2017 አሸናፊዋ አትሌት ወርቅነሽ ደገፋ በ2፡17፡41 እንደ ሩት ሁሉ ክብረወሰኑን በማሻሻል ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች፤ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በለንደን ማራቶን ያስመዘገበችውን ጊዜ በ15 ሰከንድ በማሻሻል የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ክብረወሰንን ተረክባለች፤ ሌላኛዋ ወርቅነሽ ኢዴሳ 2፡21፡05 ሰዓት ሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቅቃለች፡፡
ዋጋነሽ መካሻ፣ ስንታየሁ ለውጠኝ፣ ራህማ ቱሳ፣ ሙሉሃብት ፀጋ እና ሱሌ ኡቱራ ከአራት እስከ ስምንት ያለውን ደረጃ በመያዝ አጠናቅቀዋል፡፡
IAAF ለማራቶን ውድድሮች አዲስ የደረጃ ምደባ ሲያከናውን ለዱባይ ማራቶን የፕላቲኒየም ደረጃን በመንፈጉ፤ የውድድሩ አዘጋጅ አካል፤ አሸናፊ ለሚሆነው አትሌት ከዚህ ቀደም ይከፍል ከነበረው ገንዘብ በግማሽ በመቀነስ ዘንድሮ 100 ሺ ዶላር የሚሰጥ ይሆናል፡፡