በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ላይ የሚሰራ ዓለም አቀፍ አማካሪ ምክር ቤት ተቋቋመ
በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ላይ የሚሰራ ዓለም አቀፍ አማካሪ ምክር ቤት ተቋቋመ
አርትስ 10/04 /2011
ከመንግስት ጋር በጋራ የሚሰራው አማካሪ ምክር ቤቱ ከዓለም አቀፍና ሀገር ውስጥ የተውጣጡ ከፍተኛ ተመራማሪዎችንና ሳይንቲስቶችን ጨምሮ 134 ምሁራንን በአባልነት ይዟል።
ምክር ቤቱን ያቋቋመው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዛሬ የምስረታ ጉባዔ አካሂዷል።
በጉባኤው ላይ ሚኒስትር ዲኤታው ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ እንዳሉት የምክር ቤቱ መቋቋም መንግስት በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ያለውን የትምህርት ጥራት ለማሻሻል የጀመረውን ጥረት በብቃት ለመወጣት ያግዛል።
ለዚህም ከውጭ እና ከሀገር ቤት የተውጣጡ ከፍተኛ ልምድና ተሞክሮ ያላቸው ሳይንቲስቶች፣ ተመራማሪዎችና የተለያዩ ተቋማት መሪዎች አካላት በአማካሪ ምክር ቤቱ ውስጥ እንዲካተቱ መደረጉን ገልፀዋል።
ከአባላቱ መካከል 33ቱ ከውጭ ሀገራት ታላላቅ ዩኒቨርሲቲዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት የተመረጡ ምሁራን ናቸው።
የምክር ቤቱ አባላት ዘርፉ የሚመራበትን ስትራቴጅክ እቅድና ተቋማዊ እሴት መገንባት፣ ዘርፉን ለማጠናከር በዓለም አቀፍ ደረጃ ኃብት የሚሰበሰብበትንና የትብብር ግንኙነት የሚፈጠርበትን መንገድ የማመቻቸት ሚና ይኖራቸዋል።
የአማካሪ ምክር ቤቱ ተጠሪነት ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ይሆናል፤ የምክር ቤቱን የእለት ተለት ተግባር በቅርበት የሚመራ ሴክረቴሪያትም ይቋቋማል።
በአማካሪ ምክር ቤቱ የተሰየሙት ምሁራንና ሌሎች አካላት ለመጪዎቹ አምስት ዓመታት በአማካሪነት ያገለግላሉ ኢዜአ እንደዘገበው።