loading
በኢትዮጵያ ኮሮና ወረርሽኝ የመያዝና በቫይረሱ የመሞት ምጣኔ መቀነሱ ተነገረ::

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 7፣ 2013 በኢትዮጵያ ኮሮና ወረርሽኝ የመያዝና በቫይረሱ የመሞት ምጣኔ መቀነሱ ተነገረ:: የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው ዓባይነህ በኮሮና ወረርሽኝ የመያዝና በቫይረሱ የመሞት ምጣኔ መቀነሱን አስታውቋል፡፡

የቫይረሱ ስርጭት መቀነሱ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እና ከጤና ሚኒስቴር ጋር ለ15 ወራት ሥጋት ሆኖ በዘለቀው የኮሮና ወረርሽኝ ላይ የተደረጉ የምርምር ጥናቶች በቀረበበት ወቅት ነው፡፡ የወረርሽኙ አሁናዊ የሥርጭትና የሞት ምጣኔ ማዕበሉ የመውጣትና የመውረድ ሁኔታ መሆኑን ጠቁመው በድጋሚ ሥርጭቱ እንዳያሻቅብ አሁንም ጥንቃቄ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የወረርሽኙ ሥርጭት ከፍ እና ዝቅ ማለት የተለመደ ቢሆንም፣ እንደ ሌሎች አገሮች ዋጋ እንዳያስከፍለን ቅድመ መከላከል ላይ ኅብረተሰቡ መበርታት አለበት ብለዋል፡፡

በአትዮጵያ በ2012 ዓ.ም. የትንሳዔ በዓል ግብይት ወቅት ማኅበረሰቡ ጥንቃቄ ባለማድረጉ፣ በነሐሴ ወር በተደረገው የዳሰሳ ጥናት ወረርሽኙ ተዛምቶ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ አሁንም ያለው የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ዝቅ ሲል ይዞ የሚመጣው የወረርሽኝ ማዕበል ከፍ ሊል ይችላል ብለዋል፡፡ ስለዚህ የሚከናወኑ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ መሰባሰቦች የሥርጭት ምጣኔውን ከፍ ስለሚያደርጉ፣ አሁንም መሰባሰብን መቀነስ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡ በተጨማሪም ማኅበረሰቡ ስለቫይረሱ ያለው ግንዛቤ 99 በመቶ መድረሱን፣ ለዚህም 34 በመቶ ከሬዲዮ፣ 47 በመቶ ከቴሌቪዥን፣ 20 በመቶ ከማኅበራዊ ድረ ገጾችና አምስት በመቶ ደግሞ ከሃይማኖት ተቋማት መሆኑን በጥናት መረጋገጡን ምክትል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *