loading
በአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ የተወሰኑ ውሳኔዎች የኢትዮጵያን ጥቅም ያስከበሩ መሆናቸው ተገለጸ

በአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ የተወሰኑ ውሳኔዎች የኢትዮጵያን ጥቅም ያስከበሩ መሆናቸው ተገለጸ

ኢትዮጵያ በቅርቡ ያጸደቀችው የስደተኞች አዋጅም በህብረቱ አባል ሃገራት ዘንድ አድናቆት ተችሮታል።

ማክሰኞ የካቲት 4 ቀን በተጠናቀቀውና ”ዘላቂ መፍትሄ በአስገዳጅ ሁኔታ ለሚፈናቀሉ የአፍሪካ ስደተኞች፣ ከስደት ተመላሾች እና የውስጥ ተፈናቃዮች” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ለሁለት ቀናት በተካሄደው 32ኛው የአፍሪካ ህብረት መደበኛ የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተወሰኑ ውሳኔዎች የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ያስጠበቁ ነበሩ ብሏል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ  ።

የአፍሪካን አህጉር ህዝቦች መፃዒ እድል የሚወስኑ በርካታ ውሳኔዎች ተላልፈውበታል በተባለው በዚሁ ጉባዔ ላይ ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች የኢትዮጵያን ጥቅም ያስጠበቁ እንዲሆኑ በአገራችን በኩል ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስራ ተስርቷል ብሏል ቃል አቀባዩ። በዚህም አመርቂ ውጤት ተገኝቷል ነው ያለው።

በጉባኤው ከተወሰኑ ውሳኔዎች መካካል የሰው ሃይል ሪፎርም አንዱ ሲሆን የሪፎርሙ አካል የነበረው የሰው ሃይል ቅጥር የየአገሮችን ኮታ መሰረት ባደረገ መልኩ እንዲሻሻል የሚለው አንቀጽ ጸድቋል ተብሏል።

ይህ ሃሳብ ተቀባይነት አግኝቶ መጽደቁ በአሁኑ ወቅት በህብረቱ ውስጥ በአስተዳደርና ጠቅላላ አገልግሎት ዘርፍ በሎካል መደብ ላይ እየሰሩ ያሉ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ሰራተኞች ሳይፈናቀሉ እንዲቀጥሉ አስችሏል።

በቀጣይ በርካታ ኢትዮጵያዊያን በዚሁ ዘርፍ በአፍሪካ ህብረት ውስጥ የስራ እድል እንዲያገኙ አስተማማኝ መሰረት ለመጣልም አስችሏል ተብሏል። በተያያዘ ዜናም ኢትዮጵያ ያጸደቀችው የስድተኞች አዋጅ በመሪዎቹ ጉባኤ አድናቆት ተችሮታል።

ጉባኤው በሪፖርቱ ኢትዮጵያ በቅርቡ ያፀደቀችው አዲሱ የስደተኞች አዋጅ ወቅቱን ያገናዘበና ለአፍሪካ ብሎም ለመላው ዓለም በሞዴልነት የሚወሰድ ነው ብሎታል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒ ጎቶሬስን ጨምሮ በርካታ መሪዎች ባደረጉት ንግግር አዲሱ አዋጅ የስደተኞቹን ኑሮ ለማሻሻል ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ኢትዮጵያን ያስመስግናታል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከ900,000 በላይ ስደተኞችን በመቀበል ከዩጋንዳ በመቀጠል ከአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *