loading
በአዲስ አበባ አዋሬ ገበያ በደረሰ የእሣት አደጋ አንድ ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ወደመ ::

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2013 በአዲስ አበባ አዋሬ ገበያ በደረሰ የእሣት አደጋ አንድ ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ወደመ ::በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 በተለምዶ አዋሬ ገበያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በደረሰ የእሣት አደጋ አንድ ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል።የከተማ አስተዳደሩ የእሣትና የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት መሪ አቶ ጉልላት ጌታነህ የእሣት አደጋው ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ከሌሊቱ 10 ሠዓት ከ54 አካባቢ መድረሱን ገልጸዋል።

አንድ ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ሲወድም በተደረገው ርብርብ 10 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ማዳን መቻሉን እንዲሁም በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ተናግረዋል።አደጋው የደረሰበት አዋሬ ገበያ የሚገኙ የመኖሪያና የንግድ ቤቶች በጣም የተጠጋጉና የተገነቡባቸው ቁሳቁስም ተቀጣጣይነት ያላቸው መሆናቸው እሣቱ በፍጥነት እንዲዛመት አድርጓል ብለዋል።

እሣቱን ለመቆጣጠር 1 ሠዓት ከ50 ደቂቃ የፈጀ ሲሆን፤ 22 ተሽከርካሪዎችና 80 የእሣትና ድንገተኛ አደጋ ሠራተኞች ተሰማርተዋል፤ 130 ሺህ ሊትር ውሃም ጥቅም ላይ ውሏል።የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽኖች አባላትና የአካባቢው ማኅበረሰብም እሣቱን ለማጥፋት ርብርብ አድርገዋል።የአደጋው መንስኤና በምን ያህል ሱቆች ላይ አደጋ ደረሰ? የሚለው እየተጣራ መሆኑንም አቶ ጉልላት ተናግረዋል።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *