loading
በአውስራሊያ የተከሰተው የጎርፍ መጥለቅለቅ በርካታ ሺዎችን ከመኖሪያቸው እያፈናቀለ ነው::

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 13 ፣ 2013 በአውስራሊያ የተከሰተው የጎርፍ መጥለቅለቅ በርካታ ሺዎችን ከመኖሪያቸው እያፈናቀለ ነው:: የሀገሪቱ መንግስት እስካሁን የአደጋ ስጋት ያለባቸውን 18 ሺህ ገደማ ነዋሪዎችን ከአካባቢያቸው እንዲነሱ አድርጓል፡፡ በአውስትራሊያ የተከሰተው ጎርፍ በአስከፊነቱ ከ60 ዓመታት ወዲህ ታይቶ እንደማይታወቅ ነው ሮይተርስ የዘገበው፡፡

የኒው ሳውዝ ዌልስን እና ሌሎች አካባቢዎችን ያጥለቀለቀው ጎርፍ በቀጣዮቹ ሳምንታትም ተጠናክሮ እደሚቀጥል የአየር ሁኔታ ትንበያዎች ያመላክታሉ፡፡
ሁኔታው ባለፈው ዓመት አውስትራሊያን በሰደድ እሳት ሲያሰቃያት ከነበረው የአየር ፀባይ ጋር ፍፁም ተቃራኒ መሆኑን የሀገሪቱ ባለስልጣናት ተናግረዋል፡፡
በሳምንቱ መጨረሻ በሲዲኒ የጣለው ዝናብ በዓመቱ ከዘነበው ከባዱ ተብሎ የተመዘገበ ሲሆን፤ በሰሜናዊ የሀገሪቱ ዳርቻዎች የተመዘገበው የዝናብ መጠንም ባለፉት ወራት ከጣለው በሶስት እጥፍ ይበልጣል ነው የተባለው፡፡

በተለይ በምስራቃዊ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከሰኞ ጀምሮ ባሉት ቀናት በከባድ ዝናብ ሊመቱ እንደሚችሉ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል፡፡ በምእራብ ሲዲኒና አካባቢዋ የተከሰተው የጎርፍ አደጋ እንደ አውፓዊያኑ አቆጣጠር ከ1960 ወዲህ አጋጥሞ እንደማያውቅ ነው የሀገሪቱ ባለስልጣናት የሚናገሩት፡፡ በኒው ሳውዝ ዌልስ እንዲሁም በኩዊንስላንድ በርካታ ቦታዎች እስከ መጭው ረቡዕ ድረስ ባለው ጊዜ ከፍተኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ ሊያጋጥም ይችላል የሚል ስጋት መኖሩ ተነግሯል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *