loading
በአማራና ትግራይ ህዝቦች መካከል ግጭትም የግጭት ፍላጎትም የለም አሉ የሁለቱ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች

በአማራና ትግራይ ህዝቦች መካከል ግጭትም የግጭት ፍላጎትም እንደሌለ የሁለቱ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ገለጹ።
የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በተለያዩ አካባቢዎች ሲያደርጉት የነበረውን የሰላም ጉዞ አስመልክቶ በአዲስ አበባ የማጠቃለያ መድረክ አካሄደዋል።
በመድረኩ ላይም ከተለያዩ የሀይማኖት ተቋማት የተውጣጡ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የክልል ርእሳነ መስተዳድሮች ተሳትፈዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ “የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በተለያዩ አካባቢዎች የሰላም አጀንዳ ይዘው በመንቀሳቀሳቸው ሊመሰገኑ ይገባል” ብለዋል።
ምክንያቱ ደግሞ ሰላም ከሁሉም በፊት አንገብጋቢ አጀንዳ በመሆኑ ነው ሲሉም አቶ ገዱ ተናግረዋል።
“ሰላም ለራሳችን፣ ለሀገራችን፣ ለምንመራው ህዝብ፣ ለልጆቻችን አስፈላጊ ነው” ያሉት አቶ ገዱ፥ “ምክንያቱም የሰላም መጥፋት ምን ያክል ጉዳት እንዳለው ስለምናውቅ ነው” ብለዋል።
አቶ ገዱ በመግለጫቸው፥ “የአማራ ክልል ህዝብ ከሁሉም ጋር ሰላም መሆን ይፈልጋል፤ ከህዝቡ ጋር በነበራችሁ ውይይትም ይህንን ማረጋገጥ ችላቹዋል፤ እኔም ለሰላም በቁርጠኝነት ለመስራት ዝግጁ ነኝ” ብለዋል።
“የአማራ ህዝብ እና የትግራይ ህዝብ የጋራ ታሪክ እና እሴት ያለው ህዘብ ነው” ያሉት ርእሰ መስተዳድር አቶ ገዱ፥ አንዱ አንዱን የሚፈራ ሳይሆን አንዱ በአንዱ የሚኮራ ህዝብ ነው ብለዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህ እየተሸረሸረ መምጣቱንም ርእሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በመግለጫቸው አንስተዋል።
የአማራ ህዝብ ከትግራይ ህዝብ ጋር ግጭት አይፈልግም፤ ይልቁንም በመካከላቸው ያለው አለመግባባት ሰላማዊ በሆነ መንገድ እና በውይይት እንዲፈታ ይፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል።
“እኔም የአማራ ህዝብ መሪ እንደመሆኔ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ በቁርጠኝነት እሰራለሁ” ሲሉም አረጋግጠዋል።
የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል በበኩላቸው፥ የሀይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ሰላምን ለማምጣት ላደረጉት ጥረት ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል።
የሀይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች እዚህ ውስጥ በመግባታቸው ሀዘን ተሰምቶኛል፤ ምክንያቱም እኛ ፖለቲከኞች መስራት የነበረብንን ባለመስራታችን ነው እዚህ ውስጥ የገባችሁት ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት እርስ በእርስ ያለው ጥላቻ፣ ፍርጃ፣ ጥቃት እና መፈናቀል በጣም አሳፋሪ ነው፤ ፖለቲካን ትተን በፊት የነበሩ የኢትዮጵያ መሪዎችን ከተመለከትን ከራሳቸው አልፎ ከሌሎች ሀገራት የተፈናቀሉትን በክብር ተቀብለው የማስተናገድ እሴት ነበረን፤ ይህንን እያለን እንዴት እዚህ ውስጥ ገባን ሲሉም ጠይቀዋል።
ከዚህ በፊት ለተፈጠሩ ችግሮች የእከሌ ነው የሚባል ነገር የለም ለሰላም ቅድሚያ እንሰጣለን ብለዋል።

ምንጭ ፋና

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *