loading
በትግራይ ኤርትራዊያን ስደተኞች ደህንነታቸው አደጋ ላይ መሆኑ ተገለፀ::

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 8፣ 2013 በትግራይ ኤርትራዊያን ስደተኞች ደህንነታቸው አደጋ ላይ መሆኑ ተገለፀ:: አሸባሪው ህወሓት ስደተኞች በሰፈሩባቸው አካባቢዎች ጥቃቶች መክፈቱን የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡ ኤጀንሲው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ባለከው መግለጫ እንደገለጸው፤ ህወሓት የመንግስትን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ውድቅ አድርጎ ስደተኞች ላይ ጥቃት እየፈጸመ ነው።

በዚህ የህወሓት ጥቃት ምክንያት በማይ-ዓይኒ እና በአዲ-ሐሩሽ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙት ኤርትራዊያን ስደተኞች ደህንነታቸው አደጋ ላይ እንደወደቀ ኤጀንሲው አስታውቋል። በዚህም የተነሳ ደህንነታቸው ሊጠበቅ ወደሚችልባቸው አካባቢዎች እንዲዛወሩ፣ በድጋፍ ላይ የተመሰረተ የከተማ ስደተኝነት እውቅና እንዲሰጣቸው እና ወደ ሶስተኛ ሀገር እንዲዛወሩ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጥያቄ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ ብሏል፡፡

በችግሩ ዙሪያ ከስደተኞች ተወካዮች ጋር ተከታታይ ውይይቶችን ማካሄዱን የገለጸው ኤጀንሲው፤ ስደተኞቹን በአዲስ መጠለያ ጣቢያ ለማስፈር እና በድጋፍ ላይ የተመሰረተ የከተማ ስደተኝነት እውቅና ለመስጠት ጠንክሮ እየሠራ ይገኛል ብሏል፡፡ በመንግሥት በኩል እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን እና ለውጦችን በመረዳት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ውጤታማ እና ተጨባጭ ድጋፎችን በማድረግ ስደተኞችን በአዲስ መጠለያ ጣቢያ የማስፈሩን ሂደት ለማፋጠን የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙ ጥሪ እናቀርባለን” ሲልም ኤጀንሲው በመግለጫው አስታውቋል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *