ቅዱስ ጊዮርጊስ የሊጉን መሪነት የሚያጠናክርበትን ዕድል አበላሽቷል
ቅዱስ ጊዮርጊስ የሊጉን መሪነት የሚያጠናክርበትን ዕድል አበላሽቷል
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ14ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በዕለተ ዕሁድ ሁለት ግጥሚያዎች ተካሂደዋል፡፡
በሳምንቱ ተጠባቂ በነበረው ግጥሚያ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአዲስ አበባ ስታዲየም ፋሲል ከነማን አስተናግዶ በ1 ለ 1 አቻ ውጤት ተለያይቷል፡፡
ግብ በማስቆጠር ረገድ ቀዳሚ የሆነው እንግዳዎቹ አፄዎቹ ሲሆን የቡድኑ አጥቂ አብዱራህማን ሙባሪክ አስቆጥሯል፤ የመጀመሪያው አጋማሽ ከመጠናቀቁ በፊት ፈረሰኞቹ በሙሉዓም መስፍን ግብ አቻ በመሆን ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡
ከዕረፍት መልስ ሁሉቱም ቡድኖች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም፤ ሙከራቸው ፍሬ ማፍራት አልቻለም፡፡
ጊዮርጊስ ከተከታዮቹ ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማስፋት የነበረውን ዕድል ሲያመክን፤ ፋሲል በተከታታይ የአቻ ውጤትን እያስመዘገበ ይገኛል፡፡
ክልል ላይ ሀዋሳ ከተማ በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ስታዲየም ከድሬዳዋ ከነማ ጋር ተጫውቶ፤ ገናናው ረጋሳ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ እንግዳው የምስራቁ ቡድን 1 ለ 0 ረትቷል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ13 ጨዋታዎች ላይ በሰበሰባቸው 25 ነጥቦች ሊጉን እየመራ ይገኛል፤ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ይቀረዋል፡፡ ሶስት ተስተካካይ ጨዋታዎች ያሉት መቐለ 70 እንደርታ በ11 ጨዋታዎች 23 ነጥቦችን ይዞ ሁለተኛ እንዲሁም ሲዳማ ቡና በተመሳሳይ 23 ነጥቦች በግብ ክፍያ አንሶ ሶስተኛ እና ሁሉንም የሊግ ግጥሚያዎች ያከናወነው ኢትዮጵያ ቡና በ22 ነጥብ አራተኛ ደራጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
መከላከያ በ10፣ ደቡብ ፖሊስ በ8 እና ደደቢት በ4 ነጥቦች ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን የመከላከያው ምንይሉ ወንድሙ በ9 ጎሎች እየመራ ነው፤ አማኑኤል ገብረሚካኤል ከመቐለ፣ አዲስ ግደይ ከሲዳማ፣ ታፈሰ ሰለሞን ከሀዋሳ እና ዳዋ ሆቴሳ ከአዳማ በዕኩል 8 ጎሎች ይከተላሉ፡፡