ሽመልስ በቀለ በምስር ኤል መቃሳ የመጀመሪያ ጨዋታ ቡድኑን ከመመራት ተነስቶ እንዲያሸንፍ አድርጓል፡፡
ከቀናት በፊት ከፔትሮጀት ወደ ምስር ኤል መቃሳ በሶስት ዓመት ከግማሸ ውል የተዛወረው ሽመልስ በቀለ፤ ትናንት በግብፅ ፕሪምየር ሊግ አዲሱ ክለቡ አል ሞካውሎን አል አረብ ጋር ተጫውቶ 2 ለ 1 ሲረታ ሁለቱንም ግቦች አስቆጥሯል፡፡
በሊጉ የ19ኛ ሳምንት መርሀግብር ሁለቱ ቡድኖች ሲገናኙ፤ በሌላ ስሙ አረብ ኮንትራክተርስ ተብሎ የሚጠራው ቡድን በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ በመሀመድ ሳሚር የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ቀዳሚ ሲሆን፤ በሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮጵያዊው ሽመልስ በቀለ ተቀይሮ በመግባት በሰባት ደቂቃ ውስጥ የመጀመሪያ ጠንካራ የጭንቅላት ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ ሲሆን በተጨማሪም የጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ያስቆጠራት ሌላ ግብ ምስል ኤል መቃሳዎች በጣም አስፈላጊ ሶስት ነጥብ እንዲያሳኩ አግዟቸዋል፡፡
በዚህም ሽመልስ በሊጉ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት በፔትሮጀት ያሉትን ሰባት ጨምሮ ማለት ነው አሁን ላይ 9 ደርሰዋል፡፡
ምስር ኤል መቃሳም በሊጉ የደረጃ ሰንጠራዥ በ30 ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፤ በቀጣይ የሊጉ ሁለት ጨዋታዎች ግን ከግብፅ ሀያላኑ አል አህሊ እና ዛማሊክ በተከታታይ የሚገጥም ይሆናል፡፡
ትናንት በተከናወኑ ሌሎች ጨዋታዎች ኤል ኢንታግ ኤል ሃርቤ ከ ፒራሚድስ 1 ለ 1 አቻ ሲለያዩ፣ ኖጎም ስሞሃን 4 ለ 0 አሸንፏል፡፡ አል አህሊ ከ አል ማስሪ ሊያደርጉት የነበረው ግጥሚያ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል፡፡
ሊጉን ዛማሊክ በ41 ነጥብ ይመራል፤ ፒራሚድስ በ35 ይከተላል፡፡
ENPPI፣ ኢስማይሊና ፔትሮጀት ደግሞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ተቀምጠዋል፡፡