loading
ስፔናዊው አጥቂ ፈርናንዶ ቶሬስ ከእግር ኳስ ራሱን ማግለሉን አስታውቋል፡፡

ስፔናዊው አጥቂ ፈርናንዶ ቶሬስ ከእግር ኳስ ራሱን ማግለሉን አስታውቋል፡፡

የቀድሞው የአትሌቲኮ ማድሪድ፣ ሊቨርፑል እና ቼልሲ ተወዳጅ ተጨዋች ፈርናንዶ ቶሬስ በ35 ዓመቱ እግር ኳስ መጫወት ማቆሙን ይፋ አድርጓል፡፡

ቶሬስ የ18 ዓመት የፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ህይወቱን መግታቱን እና የጃፓኑን J1 ሊግ ሳጋን ቶሱ ክለብ ደግሞ የመጨረሻው ሆኗል፡፡

ለሀገሩ ስፔን ብሔራዊ ቡድን በስድስት ትልልቅ ውድድሮች ላይ በማገልገል፤ 110 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ ተጫውቷል፤ 38 ጎሎችንም አበረክቷል፡፡ የብሔራዊ ቡድኑም ሶስተኛው ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ነው፡፡ የዩሮ 2008 እና 2012 እንዲሁም የ2010 የዓለም ዋንጫዎችንም ከሀገሩ ልጆች ኮከቦች ጋር በመሆን አሳክቷል፡፡

‹‹ ከ18 አመርቂ ዓመታት በኋላ የእግር ኳስ ህይወቴ ተጠናቅቋል›› ሲል ቶሬስ በትዊተር ገፁ አስፍሯል፡፡

ተጫዋቹ እግር ኳስን በአትሌቲኮ ዴ ማድሪድ መጫወት የጀመረ ሲሆን በ2007 በ20 ሚሊዬን ፓውንድ ሂሳብ ወደ እንግሊዙ ሊቨርፑል በማምራት በቀዩ ማሊያ 142 ጨዋታዎች ላይ 81 ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል፡፡ ያለውን ልዩ ክህሎትም በትልቁ በዚሁ በመርሲ ሳይዱ ክለብ ማሳየት ችሏል፡፡

በ2011 ደግሞ በጊዜው የብሪታኒያ የተጫዋቾች የዝውውር ክብረወሰን በሆነ የ50 ሚሊዬን ፓውንድ ዋጋ ወደ ቼልሲ በማቅናት፤ ከሰማያዊዎቹ ጋር እስከ 2014 ድረስ በመቆየት በ172 ጨዋታዎች ተሰልፎ 45 ጎሎችን በማበርከት በ2012 የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ፣ በ2013 የዩሮፓ ሊግ ዋንጫ፣ የኤፍ ኤ ዋንጫ ድል አሳክቷል    ከዚያም በጣልያኑ ኤስ ሚላን የአራት ወራት የውስት ውል ቆይታ ካደረገ በኋላ፤ በ2014 ወደ ቀድሞ ክለቡ አትሌቲኮ ማድሪድ በመመለስ በ2017/18 ዩሮፓ ሊግ ዋንጫን ሲያነሳ፤ በ2015/16 ቻምፒዮንስ ሊግ ከቡድኑ ጋር ሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቅቋል፡፡

ከአትሌቲ ጋር ዩሮፓ ሊግ ካሳካ በኋላ ወደ ጃፓን ሊግ አምርቷል፡፡ በፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ህይወቱ በ756 ጨዋታዎች 260 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል፡፡

በእግር ኳስ ህይወቱ በግል ከወጣትነቱ ጀምሮ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ኮከብ እየተሰኜ ያደገ ሲሆን በ2007/08 እና በ2008/09 በተከታታይ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ምርጥ ቡድን ስብስብ ውስጥ ተካትቷል፤ በሊጉ የወሩ ኮከብ ተጫዋች፤ የአውሮፓ ምርጥ ቡድን ስብስብ ውስጥ መካተት፣ የፊፋ ምርጥ ቡድን እና ተጫዋቾች ዝርዝር ውስጥ በመካተት ክብር አግኝቷል፡፡  

 

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *