loading
ኤርትራዊያኑ ከ 21 ዓመታት በፊት ከኢትዮጵያ ትተውት የሄዱትን የዕቁብ ብር ተረከቡ፡፡

ኤርትራዊያኑ ከ 21 ዓመታት በፊት ከኢትዮጵያ ትተውት የሄዱትን የዕቁብ ብር ተረከቡ፡፡

ኤርትራዊው ከ21 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ይጥሉት የነበረ የዕቁብ ብር ከ50 በመቶ ወለድ ጋር ጠብቋቸዋል፡፡

‹‹አደራ የበላ በመሬትም ሆነ በሰማይ እረፍት የለውም›› ይላሉ ኢትዮጵያውያን በልማዳቸው ስለአደራ አክባሪነታቸው ሲናገሩ፤ ሌባ እንኳ በአደራ የተሰጠውን እንደማያጎድል የሚታመንባት ሀገር ናት ኢትዮጵያ፡፡

ይህንንም በተግባር ያስመሰከረ ታሪክ ከባህርዳር ሰምተናል፡፡

አቶ ፀሐዬ ኃይሉ ይባላሉ፡፡  ሰዉየዉ ከ1961 ዓ.ም ጀምሮ ማረፊያቸውን በጭስ ዓባይ አድርገው ሻይ ቤት በመክፈት ለጎብኝዎች እና ለአካቢቢው ኅብረተሰብ ሻይ በመሸጥ ይተዳደሩ ነበር፡፡

በሂደት ደግሞ ከጭስ ዓባይ ወደ ባሕር ዳር ከተማ ተዛወሩ፡፡ አቶ ፀሐዬ ባሕር ዳር ከተማ እያሉ አምስት ልጆችን ወልደዋል፡፡ አቶ ፀሐዬ በባሕር ዳር ከተማ ሲኖሩ አባ ግዛቸው ተሰማ የሚባሉ አባት ከሚመሩት እና ከመሠረቱት ዕቁብ ውስጥ በየሳምንቱ ዕቁብ ይጥሉ ነበር፡፡ 32ሺህ ብር ዕቁብ እንደጣሉ በድንገት በኤርትራና ኢትዮጵያ መሀል በተፈጠረ ግጭት  ከኢትዮጵያ ወጡ፡፡
የሁለቱ ሀገራት ፀብ ‹‹ዛሬ ይረግብ ወይስ ነገ?›› በማለት ሲጠባበቁ አባ ግዛቸው እቁቡን ሳያስረክቡ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ ነገር ግን አደራ በልተው አላረፉም፤ የሰውን ንጹሕ ገንዘብ አደራ ‹‹ለቀሪ ሰዎች እንድትሰጫቸው›› በማለት ለሚስታቸው ኑዛዜ አስቀምጠው ነበር ያለፉት፡፡

ባለቤታቸውም ለአቶ ዘመነ አባተ እና ለአቶ ተስፋ እስከዚያ ገንዘቡን አስረከቡ፡፡ አቶ ዘመነ የዕቁቡ ዋና ፀሐፊ፣ አቶ ተስፋ ደግሞ ሊቀ-መንበር ሆነው ያገለግሉ ነበር፡፡

እኝህ ሁለት ሰዎች ‹‹አደራ ከሰማይ ይርቃል፤ ቢበሉት እኳን ያንቃል›› በማለት ገንዘቡን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስቀምጠው የዕርቅ ዘመን መጠባበቅ ጀመሩ፡፡

ተስፋ አለመቁረጥ፣ ቃልም አለመሻር መልካም ነው እና ተስፋ ያረጉት ዘመን ደርሶ ገንዘቡን ለባለቤቱ ከ21 ዓመታት በኋላ አስረከቡ፡፡

ከአብመድ እንዳገኘነዉ መረጃ ከዓመታት በፊት ያስገቡት ገንዘብ ወደ 48ሺህ 4መቶ 62 ብር ከ60 ሳቲም ከፍ ብሎ በባንክ ቤት ተገኘ፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *